Friday, April 21, 2017

ባላገር የሚመራቸው ከተሞች

(ከስናፍቅሽ አዲስ)
* * * * *
(ባላገር የሚመራቸው ከተሞች)
-
በእርግጥ ባለሀገር አከብራለሁ፡፡ ባላገርም ቢሆን በስፍራው ሸጋና ውብ ነው፡፡ ያለ ስፍራው ሁሉም መልከ ጥፉ ስለመሆኑ ሙግት የሚገጥመኝ ያለ አይመስለኝም፡፡ ጭልጥ ያልኩ ከተሜ ነኝ ባይ በገጠር መንደሮች ውስጥ የለየለት ኋላ ቀር መሆኑን የሚነግሩት ለአኗኗሩ እንግዳነቱን የሚያሳዩ ጠባዮች ናቸው፡፡ እናም ይህቺ ሰው መደባዊ ናት እንዳትሉኝ፡፡
-
ብዙ የኢትዮጵያ ከተሞች ከዘመን ዘመን እንደ ነበሩ ናቸው፡፡ ከተሜነት በከተማዎቻችን አኗኗር እንግዳና ብርቅ ሆኗል፡፡ ወይ ያልገጠሩ ወይ ያልከተሙ መንደሮች እየበዙ ነው፡፡
ህንጻዎች ተገንብተው፣ ከተሞቹ መናገሻ ሆነው፡፡ የፖለቲካ ማዕከል እየተባሉ እንኳ የከተሜ ጠባይ ናፍቋቸዋል፡፡ የብዙ ከተሞቻችን ችግር ግን ይህ ስርዓት በከተሜዎች ከተሞች እንዲመሩ አለማድረጉ ይመስለኛል፡፡
-
የስልጣን ባለቤትነት የብሔሮች እና ብሔረሰቦች መብት እንደሆነ እናውቃለን እናምናለን፤ ያልተስማማንበት ሁሉ ስልጣን ለሁሉ የገጠር ልጆች የሚለውን ገጠርኛ ብሂል ከከተማ ለማስማማት የሚደረገውን ጥረት ነው፡፡
-
እኔ የአዲስ አበባ ልጅ ነኝ፡፡ አዲስ አበባ ኦሮሞም ሆነ አማራ፣ ትግሬም ሆነ ደቡብ ሳያሳስበኝ በየቱም ዘር ብትመራ ግድ አይሰጠኝም፡፡ ግን እሳት የላሰ የከተማ ልጅ እፈልጋለሁ፡፡
-
ዩኒቨርሲቲ ሲሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ በመኪና ያልተጫነ፤ የከተሜነት ምኞቱ ምትክ የሌለው፤ ስለ ከተማው የሚጨነቅ፤ መስታወት ቢሮ ውስጥ ተቀምጦ የቦረቀበት መስክ የማይናፍቀው፡፡ ይሄ ነዋ ችግሬ በከተማዬ ልጅ አለመመራቴ፤ እኔ ብቻ አይመስለኝም የሀገሬ ከተሞች ናፍቆት እና ምኞት ይሄ ነው፡፡
-
ብዙ ከተሞች በብዙ የገጠር ልጆች እየተመሩ ነው፡፡ ሀገሬ ብሎ ለበዓል ገጠር የሚገባ ከንቲባ ከተማ ሲመራ ከተማው መስሪያ ቤቱ እንጂ ሀገሩ አትሆንም፡፡ እናም የመሰረተ ልማት ውጥንቅጥ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ሙስናና ብልሹ አሰራር፣ አልጠግብ ባይነት ባላደጉባት ከተማ ሲነግሱባት፣ ቤተሰብ ግብር ገብሮ ያላኖራትን ከተማ ሲያስገብሩባት የሚከሰት ይመስለኛል፡፡
-
ከተሞች ዛሬ በቆሻሻ ክምር ሲናዱ፣ በጎርፍ ሲተራመሱ፣ ጎዳናዎቻቸው ሐይቅ ሲሰሩ፣ ዛሬ የተሰራ መንገድ ነገ ሲፈርስ፣ በቂ የመኪና መንገድ ሳይተው፣ የመኪና መቆሚያዎች ሳይታሰቡ ፎቆች ሲገጠገጡባቸው ምን ይሆን ችግሩ ለማለት ያልደፈርነው እንዴት እከሌ እንዲህ ያደርጋል የምንለው የከተማችን ልጅ በወንበሩ ስለሌለ መሰለኝ፡፡
-
ምንም ቢሆን የከተማህ መሪ አንተ ስትሆን የልጅነት ምኞትህን ለማሳካት ስለከተማህ ትጨነቃለህ፤ የልጅነት ምኞትህ ከተማ ገብቶ መኖር ሆኖ ከተማ መሪ ስትደርግ ግን ከምኞትህ ፈቅ ያለው ስፍራ ላይ ነህና ሌላ ራዕይ ላይኖርህ ይችላል፡፡ ሁሉም በስፍራው ልክ ቢሆንም ያለ ስፍራው ደግሞ ልክ የሚሆንም ምንም የለም፡፡
-
በከተሞች ያለው ስራ አጥነት፣ የቤት ችግር፣ የመሬት ወረራ፣ ያልተገባ እና የከተማዋን ነዋሪዎች የሚያቆረቁዝ የብልጣ ብልጥ የገጠር ልጆች ኔት ወርክ ሁሉ መነሻው ያለ ቦታ መገኘት ነው፡፡ እናም በባላገር የሚመሩ ከተሞችን የሚታደግ አሰራር እንመኛለን፡፡

No comments:

Post a Comment

“በነውጠኛ አብዮት ሳይሆን፣ በማህበራዊ ለውጥ እንታመናለን!”