Friday, April 21, 2017

ትዝታ

(ትዝታ የአዲስ አበባ ልጅ)
* * * * *
የህዝብ ትምህርት ቤት (ዘርዓያቆብ ፣ ባልቻ ፣ አግዓዚያን ...) የተማረ ፥ ጠጠር ፣ብይ ፣ቆርኪ ተጫውቶ ያደገ፥ እቃቃ ላይ ደክሎ የሚያውቅ ፥ በፍሩት ፓንች ዴይ ፓርቲ የጨፈረ ፥ ከአዝማሪ ቤት እስከ ክለብ ሸገርን ያካለለ ፥ ድብን ብሎ ሰከሮ የሚያውቅ ፥ ቪ ኦ ኤ ፣ጀርመን፣ ኢሳት የሚከታተሉ ዘመዶች ያሉት፥ ሲጋራ አጢሶ የሚያውቅ፥ ፌስ ቡክ አካውንት ያለው፥ 24 Hours ን ሙሉ ሲዝኑን የጨረሰ ፥ በአረጋኸኝ ዘፈን ትታይ ያለ፥ ቦሌ መንገድ ወይም ብስራተ ገብርኤል አካባቢ ዎክ ያደረገ ፥ የጨረቃ ቤት የገነባ አጎት ያለው ፥ ኬር በሰራው መንገድ ላይ የተመላለሰ፥ አልሞሪካ መንፋት የሚችል ፣የአባባ ተሰፋዬን ተረት ሰምቶ ያደገ ፥ የአንበሳ አውቶብሰ ተጠቃሚ የነበረ ፥ ውይይት ላይ ተሳፍሮ ከወያላ ጋር የተጨቃጨቀ፡
-
የቀበሌ ቤት የኖረ ፥ በሰገጤ ሙድ መያዝ የሚችል ፥ ቪዲዮ ካሴት የተዋዋሰ ፥ አይፓድ የነበረው፥ ኢሜይል መጠቀም በ ሆት ሜይል የጀመረ ፥ የተመዘገቡ ከስምንት ያላነሱ ገርል ፍሬንድ የነበረው ወይም ያለው ፥ ቀበና፣ ግንፍሌ ወይም አቃቂ ወንዝ የዋኘ፥ ዲስቲቪ ከመምጣቱ በፊት ሊቨርፑልን የሚያወቅ ፥ የሰፈር ልጅ ሸሌ ሻወር ሲወስድ ውሃ ያፈሰሰ ፥ የሲዲኒ ሸልድን እና ዳኔላ ስቲል መፅሃፎችን ዋናውንም ትርጉሙንም ያነበበ ፥ ባለ ጉዳይ ፣ ገመና እና አካፑልኮን የተከታተለ ፥ተነሳ ተራመድን ክንድህ አበርታን የዘመረ፥ የኦሾ መፅሃፎችን ተዋውሶ ያነበበ፡፡
-
ሰርቆ ተይዞ የሚያውቅ ፥ ላፍቶ መሬት ሲመሩ ገጠር ነው ብለው ከተው ቤተሰቦች የተገኘ ፥ የሽቦ መኪና ያሽከረከረ ፥ የቴዲ አፍሮን ኮንሰርት ገብቶ የሚያውቅ ፥ ለሰፈር ማጄ (ጉልበተኛ) የተላላከ ፥ መሃልዬ መሃልዬ ዘ ካዛንቺሰን እና ትኩሳትን ከሁለት ጊዜ በላይ ያነበበ ፥ እናቱ ወይ አባቱ መሠረተ ትምህርት ያስተማሩ ፥ ሲኒማ ኢትዮጵያ ፣ አምፒር ፣ ኤድና ሞል እና አለም ሲኒማ ያዘወተረ ፥ ቢያንስ ሶስት ምርጫ የመረጠ ፥ ቢያንስ ሁለት ብሄራዊ መዝሙር የሚያውቅ ፥ ለሽቀላ ታላቁን የሰፈር ልጅ ጠርቶ የካ (አንድ ብር ) የፈለጠ ፥ የፖለቲካ አቋሙን የህዝብን የልብ ትርታ አድምጦ መቀያየር የሚችል (እትብቴ/የአባቴ አጥንት ጠራኝ ምናምን ብሎ አሰስ ገሰስ የማይዘበዝብ)፡፡
የአዳም ረታን መፅሃፍ መረዳት የሚችል ፥ ሊብሮ እና ኢንተር ስፖርትን ያነበበ ፥ ፓስቲ በውሃው ጀላቲ (በረዶ) እያጣጣመ የበላ ፥ ለገዳዲ ሬዲዮ ያደመጠ ፥ የኩኩ ሰብስቤ ጨሌዎች ፋሽን አንደነበሩ የሚያውቅ ፥ አረንቻታ ምንድን ነው? ሲባል ግራ የማይገባው ፥ ካርታ እንጀራ በወጥ የተጫወተ ፥ የተመረጡ የአዲስ ጉዳይ መፅሄቶች ያሉት ፥ ለእንቁጣጣሽ ስዕል ጨርቆስ ሄዶ ቀለም የገዛ ፥ ኮንዶሚኒየም የተመዘገበ ፥መርቅኖ ተፈላስፎ የሚያውቅ ፥ በማማ እና በሾላ የወተት ላስቲክ ኳስ የሰራ ፥ ሰኔ 30 የተፈነከተ እና የፈነከተ ፥ ሹገር በርገር (ዳቦ በስኳር) ሱቅ በር ላይ ቆሞ የበላ ፥ ቦሌ ፣ ዳትሰን ሰፈር ፣ቺቺኒያ ፣ ኦሎምፒያ ፣ፒያሳ ፣ ስንጋ ተራን አብጠርጥሮ የሚያውቅ ፥ ደስቶ ፊንገር የተጫወተ ፥ ዲቪ ሞልቶ የሚያውቅ ፥ የተፋታች እህት ያለችው ፥ ደላላ ዘመድ ያለው ፥ ሳይክል ለመንዳት ስታዲየም የሄደ ፥ ደራርቱ አና ሃይሌ ሲመጡ ቦሌ ሄዶ የተቀበለ ፥ ለቆራሌው እቃ ሸጦ የሚያውቅ፡፡
-
(ከአልአዛር ወልዴ ገፅ የተወሰደ)

No comments:

Post a Comment

“በነውጠኛ አብዮት ሳይሆን፣ በማህበራዊ ለውጥ እንታመናለን!”