Friday, April 21, 2017

የሸነግ አቋም

ይህ የሸነጋዊነትና የሸነግ አቋም ነው::

ከአራቱ የሃገር ምሰሶዎች አንዱ.......

(ክቡር መተኪያ ሃይለሚካኤል)

ሁሉም ሙያ በራሱ ክብር የሚሰጠውና የማይናቅ ቢሆንም በተለየ ሁኔታ ግን አራት የአንድነት አውድ ሆነው ሃገርን እንደ ድንኳን ወጥረው ያቆሙ የህልውና መሰረት የሆኑ ሙያዎች አሉ::



የመጀመሪያው ሃኪምነት ነው::ሰው ከፈጣሪ በታች ድህነትንና ጤንነትን አግኝቶ ረዥም እድሜ በምድር ላይ እየኖረ ለመመላለስ ህክምና ግድ ይለዋል:: (ቅዱስ ሉቃስም ሃኪም ነበር)

ሁለተኛው ደግሞ ገበሬነት ነው::ሰው ሳለ በህይወቱ ከመሰረታዊ ነገሮች አንዱና ዋነኛው ምግብ ስለመሆኑ የሃገሬ ሰው “እንኳን ሰው ጆንያም እህል ሲሞላው ነው እሚቆመው”እንዲል መሬቱን አርሶ ከብቱን አርብቶ እህል እያበላ ወተት እያጠጣ የሚያኖረን እርሱ ገበሬው እንጂ ሌላ ማን ነው?::(ህዝበ እስራኤል ያይቆብም ገበሬ ነበር)


ሶስተኛው የሃገር ካስማ ወታደር ነው::“ወጥቶ አደር” ስለ ወገኑ ስለ ሃገሩ ስለ ነጻነታችን ዳግመኛ የማያገኛትን ህይወቱን የሚሰዋ :አጥንቱን የሚከሰክስ: ስጋውን የሚቆርስ: ደሙንም የሚያፈስ: ሃገር ሊወር የመጣን ወራሪ “ሬሳዬን ተራምደህ ካልሆነ እምቢኝ”የሚል ስለራሱ ሳይሆን ስለሌላው የሚኖር እርሱ ወታደር ነው:: (የብሩክታዊት አዳኝ ጊዮርጊስም ወታደር ነበር)


አራተኛውና ዋነኛው ሙያ መምህርነት ነው::መምህር ትውልድን እንደ ሸክላ አቡክቶ የሚጋግርና የሚቀርጽ የአንድ ሃገር ህልውና ከሆኑት ሙያዎች ዋነኛው እርሱ መምህርነት ነው::ድሮ ድሮ የምንወደው መምህር የሚያስተምረውን ትምህርት እንድንወድ: የምንጠላውም መምህር ትምህርቱን እንድንጠላ ያደርገን እንደነበር ሁላችንም እናስታውሳለን::(ክርስቶስን ረቡኒ ወይንም መምህር ሆይ ይሉት ነበር)::


እናም በዚህ አመት ከሰማናቸው ዜናዎች ሁላ እጅግ አስደሳቹ ዜና የመምህራን ከፍተኛ የደሞዝ ጭማሪ ነው::ይበል እሚያሰኝ ነው::እንደገና ሰሞኑን ደግሞ ለመምህራን እጅግ ተመጣጣኝ በሆነ ክፍያ የኮንዶሚኒየም ቤቶች መንግስት መስጠት መጀመሩ ደግሞ በድጋሚ ሰምተን እልል አልን::እንደዛሬው መምህርነት እምብዛም የማይፈለግ ሙያ ከመሆኑ በፊት እጅግ የተከበረና ተወዳጅ ሙያ ሆኖ እንዲያውም በሰርግ ላይ ጭምር “የኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ ወሰደሽ አስተማሪ”እየተባለ ይጨፈር ነበረ:: (የዛሬን አያድርገውና)


ደርግ በትረ ስልጣኑን በያዘ ማግስት ያወጀው የመሬት ለአራሹ አዋጅ በጭሰኝነት ሲዳክር የነበረውን አብዛኛውን ደሃ ገበሬ ባለመሬት እንዳደረገ የማንክደው ሃቅ ከመሆኑ ባሻገር ዛሬ ዛሬ ደርጎች “ሰራናቸው” ብለው ደረታቸውን ነፍተው ከሚያወሩበት ጉዳይም ዋነኛው ይሄው “የመሬት ለአራሹ አዋጅ” ነው::ዛሬም መንግስት በታሪክ ከሰራው ስራ እንደ አንዱ ሆኖ ይመዘገብለታል ብዬ ያለጥርጥር ከማምንበር ነገር አንዱ ይሄው የመምህራን ኑሮን የሚለውጠው የደሞዝ ጭማሪና የኮንዶሚኒየም ቤት እደላ ነው::


ክብር ለመምህራኖቻችን!!::

No comments:

Post a Comment

“በነውጠኛ አብዮት ሳይሆን፣ በማህበራዊ ለውጥ እንታመናለን!”