Saturday, April 22, 2017

ግንባሩ እኛን አይወክለንም!

(Behailu Gebre Egziabiher)

* * * * *
ሰበር ዜና፦ "ግንባሩ እኛን አይወክለንም!" ሲሉ መአግ፣ ሰነግ፣ ሽነግ፣ ቁነግ፣ ሾነግ፣ ግነግ፣ ፈነግ ገለፁ።

ለዝርዝሩ ጩኸቴ ከሰፈረ ሰላም

የመሿለኪያ አንድነት ግንባር፣ የሽሮሜዳ፣ የአጣና ተራ፣ የቁጭራ ሰፈር፣ የቄራ፣ የአብነት፣ የአቧሬ፣ የካዛንቺስ፣ የሰባተኛ እንዲሁም የፈረንሳይ ነፃ አውጪ ግንባሮች ባንድ ላይ በሰጡት መግለጫ "ሸነግ እኛን አይወክለንም። አቋሙንም አንደግፍም!" ብለዋል።


በተለይ የመሿለኪያ አንድነት ግንባር ፕሬዝዳንት የሆነው ወጣት እንቡጤ ቋድር እንደገለፀው ከሆነ፣ "ሸነግ በነማን እንደሚመራ አናውቅም። እኛን የመወከል ብቃትም የለውም!" ሲል አፅንኦት ሰጥቶ ተናግሯል።
የሰባራ ባቡር ነፃ አውጪ ግንባርን ወክሎ የተገኘው ወጣት ካሮቴ ቀጭኑ በበኩሉ "ሸነግ ፖለቲካዊ አቋሙ የማይታወቅ የቅሞ አደሮች ስብስብ ነው!" ሲል ግንባሩን አጣጥሎታል።

ራሱን አአግ በማለት የሚጠራው የአጣና ተራ አንድነት ግንባር ፕሬዝዳንት ወጣት ሉሲ ባሪያው ደግሞ "ሸነግ ራሱን እስካላጠራ ድረስ የእንቅስቃሴው ተቃዋሚ ነን!" ብሏል። ወጣት ሉሲ ባሪያው አባባሉን ሲያስረዳ በሸነግ ውስጥ የተሰገሰጉ ነፍ ላቦሩዎች እና ሿሿ ሠሪዎች አሉ። ሸነግ እንደ ፓርቲ ለመቆም ከፈለገ በቅድሚያ ራሱን ከእነዚህ ወዲህ በሉዎች ማፅዳት አለበት።

የሰባተኛ ነፃ አውጪ ግንባር ተወካይ የሆነችው ወጣት ባርች ቂጦ ደግሞ የመጣችበትን ፓርቲ ወክላ እንዲህ ብላለች፤ "ሸነግ ፓርቲ ዴይ ፓርቲ ላይ የተቋቋመ ነው ይላሉ፤ በርጫ ቤት ነው የተመሠረተውም ይባላል። ቅምቀማ ላይ ነው የሚሉም አሉ። አንዳንዶች የሆነ ሰፈር ድድ ማስጫ ላይ ዱቅ ብለው አልበም የሚገልጡ አምስት ስድስት ወጣቶች የመሠረቱት ነውም ይላሉ። ሸነግ የትም ይመስረት፤ አያገባንም። ብቻ ሴቶችን በበቂ ሁኔታ ባለማቀፉ ነው ደንፉ የያዘን። አሁንም ሸነግ ሴቶችን ካላቀፈ አይነፋም። ካልነፋ ደግሞ ሸነግ እኛን በጭራሽ አይወክለንም! አዎ አይወክለንም!" (ለአንባቢያን፦ አልበም መግለጥ ማለት መንገድ ዳር ተቀምጦ ወጪ ወራጁን ማየት፣ ማድነቅ፣ መተረብ እና መቀፈል ማለት ነው)
ስብሰባው ሊያልቅ ሲል ድንገት የመጣው የአራት ኪሎ ተወካይ ደግሞ ከጀሞ ኮንዶሚኒየም መምጣቱን እና በትራንስፖርት እጥረት መዘግየቱን ጠቅሶ ይቅርታ ከጠየቀ በኋላ "ሸነግ የአራት ኪሎ ነዋሪን አይወክልም!" ሲል ንግግሩን ጀምሯል። "ለመሆኑ ሸነግ ማን ነው? ይቅርታ ይደረግልኝና ለእኔ ሸነግ የሸጎሌ ሰፈር ነፃ አውጪ ግንባር ሊሆን ይችላል። የሸገር ግን ሊሆን አይችልም። እንደ አራት ኪሎ፣ መርካቶ አሜሪካን ግቢ፣ ውቤ በረሃ፣ ሱማሌ ተራ፣ በቅሎ ቤት የመሳሰሉ ሰፈሮች ፈርሰው ነዋሪዎቻቸው የሸገርን ጥጋ ጥግ በያዙበት በዚህ ጊዜ ራሱን ሸነግ ብሎ የጠራው ፓርቲ በማን እና ለምን እንደተመሠረተ ስለማናውቅ እኛም እንቃወማለን። ሸነግ ለመሆኑ ለልማት ስለተነሱ ሰፈሮች ምንድን ነው አቋሙ ኧረ? ስለዚህ ይሄ ጉዳይ ግልፅ ብሎ እስኪገባን ድረስ ራሳችንን ከዚህ ፓርቲ አግልለናል።"

ከላይ እንዳየነው ይህ ሁሉ ፓርቲ ራሱን ባገለለበት ሁኔታ ሸነግ እንዴት ህልውናውን ጠብቆ ሊጓዝ ይችላል ብለን ለሸነግ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ጥያቄ ለማንሳት ወደ ቢሯቸው ስልክ ብንደውል ፕሬዝዳንቱ የቤተሰብ ሠርግ አለብኝ ብለው ክፍለ ሀገር እንደሄዱ ተነግሮናል።

የፓርቲውን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊንም ለማነጋገር ወደ ተንቀሳቃሽ ስልካቸው ስንደውል፣ ገጠር ያለችው አክስቴ ታማ ልጠይቅ ስለሄድኩ ስመጣ ታነጋግሩኛላችሁ! ብለው ስልካቸውን ዘግተዋል።

የፓርቲው ዋና ጸሐፊም ለቢሮ ሥራ ክፍለ ሀገር እንደወጡ ሰምተናል። እሳቸውን ከሥራ መልስ ለማነጋገር ቀጠሮ ለመያዝ ስንደውልም ከሸገር ወጣ ብላ በምትገኝ የሆነች የገጠር ከተማ ከአጎቴ የተረከብኳት መሬት አለች። እሷ ላይ አነስተኛ ቤት እየገነባሁ ስለሆነ እሷን ለማየት እሄዳለሁ። ስለዚህ አይመቸኝም ብለዋል።
አንባቢዎቻችን በቀጣይ ጽሑፋችን በቻልነው መጠን የሸነግ ፓርቲን የበላይ አካላት ሐሳብ ይዘን ለመቅረብ እንሞክራለን።

ማሰሪያ ሐሳብ፦
አቦ ሸነጎች ይመቻችሁ። አሪፍ ሙድ መያዣ ፈጠራችሁልን።
የሥነቃል ጥናት እንደሚለው እኔ ሸነግን የምጠቀመው ለማምለጭ ተግባር ነው። ("ማምለጭ" የዶክተር ፈቃደ አዘዘ ቃል ናት። ደስ ስትል!)

No comments:

Post a Comment

“በነውጠኛ አብዮት ሳይሆን፣ በማህበራዊ ለውጥ እንታመናለን!”