Saturday, April 22, 2017

ታሪክ

(1)- (ታሪክ)
.* * * * *
መቼም ትልቅ ሠው ትልቅ ነው፡፡ ነገርን በብልሃት ያስውላል፡፡ ፍርድም ያውቃል፡፡
-
በጅሮንድ(ፊታውራሪ) ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም የ20ኛውን ክፍለዘመን የኢትዮጵያ ፖለቲካ trend እንዲህ ቀለል አድርገው በትናንሽ ዓናቅጽ ይነግሩናል፡፡
.
"የአድዋ ጦርነት ከተፈጸመ በኋላ በማግስቱ የላስታ፣ የየጁ፣ የበጌምድር፣ የጎጃም፣ የወሎ ሰዎች ፈንጥዘው ወደየአገራቸው ባቋራጭ መንገድ ጉዞ ጀመሩ፡፡ አዝማቾቻቸው ብቻቸውን ቀሩ፡፡ ሸዋ ብቻ በግድም በውድም ከአለቆቻቸው ጋር ቆዩ፡፡
ምርኮኛ ባሺቡዙክ ቀኝ እጃቸውን እና ግራ እግራቸውን እየተቆረጡ ተለቀቁ፡፡ ደም እየፈታባቸው ከሞቱት በቀር፣ እየተንፏቀቁ በየአገራቸው ገቡ፡፡ ቂማቸውን በልባቸው ውስጥ አቆይተው ግራ እጃቸውን እና ቀኙን ዱሻቸውን ባንድነት እያጋጠሙ ያጨበጭባሉ፣ ይዘፍናሉ፣ ይፎክራሉ፡፡
ክላ ብሎ አንተም፣ ግራ እኔም ግራ
ሃብዚዮ እናጨብጭብ ከኔ ጋራ
ይላሉ ይባላል፡፡ አምሳ አመት ያክል ቆይተው ቂማቸውን ተወጡ፡፡ ሃማሴኖች በሸዋ የሴቶችን እንኳን ጡታቸውን ቆረጡ፡፡ ይህ ሁሉ በዕኛ እድሜ የተደረገ ነው፡፡ ለኛ አዲስ ነገር ይመስለናል፡፡ ግን በታሪክ ላይ እንደሚታየው፣ በየጊዜው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጭካኔ ሲወዳደርና ብድር ሲከፋፈል ቆይቷል፡፡
እንደዚህ አድዋ ላይ ያን ያህል ሰዎች ተላለቁና፣ ጣልያን የወሰደብንን አገር ሳናስለቅቅ ሄድን፡፡ ይህን ነገር በዚያን ጊዜ ልመለከተው አልቻልኩም ነበር፡፡ የድሉን ዋጋ ለመገመቻ የሚበቃ ዕውቀት አልነበረኝም፡፡ በአውሮፓ መማር ከጀመርኩ በኋላ እያስታወስኩት እንደ እሳት ያቃጥለኝ ጀመር፡፡ ራስ መኮንን እና ዐፄ ምኒልክ በዘመናቸው የሠሩት ሥራ ሊደነቅላቸው የተገባ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ስሕተታቸውን በኋላ እየገመትኩት መገረሜ አልቀረም፡፡ ይሁን እንጂ፣ የዚያን ግዜ ዕውቀትና ኃይል በማነሱ ይቅርታ ሊደረግላቸው የተገባ ነው፡፡ እነሱ በደከሙበት ሥራ ተጠቅመናል፡፡ በስሕተታቸውም አደጋ ተቀብለንበታል፡፡ እኛም ደግሞ እንደዚሁ ማድረጋችን አይቀርም፡፡"
-('የሕይወቴ ታሪክ (ኦቶባዮግራፊ)' ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም (ገጽ 7))
-
ትልቅ ሠው ታሪክን ሲያስተውል እና ሲፈርድ እንዲህ ነው፣ ፡፡
-
-
(2) - (አገር)
* * * * *
.
አሁንም ትልቅ ሰው ሲናገር መስማታችን ግድ ነው፡፡ ፍቱን የተባለ መጽሄት የዎርልድ ባንኩን የተከበሩ ኦቦ ቡልቻ ደመቅሳን በዝርያና ባገር ዙርያ ጠያይቋቸው ነበረ፡፡ እንዲህ ይመክሩናል፡፡
-
"ኦሮሞዎች ተበደሉ ተረገጡ በምልበት ሰዓትም የኢትዮጵያን አንድነት ምን ግዜም እፈልጋለው፡፡ ምክኒያቱም የስሜት አይደለም የሎጂክ ጉዳይ ነው፡፡ሀገሬን እወዳለው፡፡ ግን ከፍቅር ብቻ የተነሳ አይደለም እንደዛ የምለው፡፡ ለሀገራችን ሕዝቦች የሚበጀው በአንድነት መቆም ነው፡፡ ብዙ ጣጣ አለው የኢትዮጵያ መፈራረስ፤ ችግር ላይ ይወድቃሉ ብዬ አስባለው፡፡"
". . .ኦሮሞዎች እንደማንም የኢትዮጵያ ቡድን፣ ያን ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት በሚባለው ላይ ጦርነት ከፍተው ተዋግተዋል፡፡ አሸንፈዋል- ተሸንፈዋል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ እርስ በርስ ብንዋጋም ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ የታወቁ የኢትዮጵያ ነገሥታትም እርስ በርሳቸው ይዋጉ ነበረ፡፡ ማን ያልተዋጋ አለ? በአንድ ሃገር የሚኖሩ ሕዝቦች ከጥቅም ዓንጻር እርስ በርሳቸው ይዋጋሉ፡፡ ተመልሰው ግን ቤታቸው ሲገቡ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ህወሀት ኢትዮጵያዊ ነው ዛሬ፣ የዛሬ 40 ዓመትም ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡ ስለኢህ የቡድኖች መነጣጠል እና መዋጋት ኢትዮጵያዊነትን አያስቀርም፡፡ ቤዙ እዚህ ነው (መሬቱን እያመላከቱ)"
-(ፍቱን መጽሄት፤ ቅጽ 7 ቁጥር 157፤ መጋቢት 2007 (ገጽ 10-11))
-
እንዲህ ነው የትልቅ ሠው ቃል፡፡ 'እኔም ዘመዶቼም ይሄንን አገር ያገልግሉ፣ ያስተዳድሩ፣ይምሩ፣ ያልሙ፣ ያሳድጉ፣ አይበደሉ' ነው የሚለው፡፡ እንጂ ነፋስ ነፈሰ፣ እንዲህ ጎደለ፣ እንዲህ አነሰ ብሎ አገር አይከዳም፡፡
. . . አገር ካንድ ትውልድ ቁመና ማኀበረ-ፖለቲካዊ ክስተት በላይ ነውና፡፡
-
-
(ሸነግ እንኳን ለአድዋ ድል ክብረበዓል አደረሰን ልላለች)

No comments:

Post a Comment

“በነውጠኛ አብዮት ሳይሆን፣ በማህበራዊ ለውጥ እንታመናለን!”