Thursday, April 20, 2017

(ድፎ ዳቦ፥ የከሸፈ ህብሰት)

(Nahusenay Belay)

(ድፎ ዳቦ፥ የከሸፈ ህብሰት)

* * * * *

እዉነተኛ የድፎ ዳቦ ታሪክ
ይህ በርካታ የታሪክ ድርሳናት አገላብጬ፣ እምቅ አእምሮየን ጨማምቄ የፃፍኩት እዉነተኛ ታሪክ ስለሆነ ሁሉም ሊያነበው ይገባል።

-

የዘር ሀረጓን ከአክሱማዉያኑ ቅዱስ ያሬድና ከፈላስፋው ዘርአያቆብ የሆነች ወለተ ሰንበት የተባለች የአክሱም ሰው እጅግ በጣም ምስጉን የቤተ መንግስት ምግብ ቤት ሃላፊ ነበረች። ተግታ እምትፀልይ እና እምታስቀድስ የተባረከች ሴት ስለነበረች አንድ ቀን በህልምዋ አንድ ነገር አየች። ያየችዉን ነገር ወደ ተግባር ቀይራ ህብስት የሚባል እንደ እስፖንጅ የለሰለሰ፣ መልኩ የሚያምር፣ ንጣቱ የሚገርም አዲስ ምግብ ፈጠረች። ይህ የሆነው በ 257 ዓ.ዓ ነው።

-

ከዛ ግዜ ጀምሮ ተጋሩ ህብስት መለያቸው፣ የህብስተ መና ተምሳሌት፣ የጥበብ ልቀት መለክያ አድርገው ይወስዱታል። እንደዉም በ 1438 ዓ.ም ቢንታልኮስ የተባለ ግሪካው ጎብኚ
እኒህ አክሱማዉያን በጣም ይገርማሉ
ስንዴዉንም ስፖንጅ ማድረግ ይችላሉ
ብሎ ተቀኝቶ ነበር ይባላል። ያኔ ስንዴን ወደ መብል የቀየሩ ህዝቦች እምብዛም አልነበሩም። በተጋሩ ብቻ ታጥሮ የተያዘው የህብስት ጥበብ ታድያ ባንድ አጋጣሚ የሸዋን ቀልብ ገዛ።

- - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - -

መተማ (እምባየ መጣ!)
በመተማው ጦርነት አፄ ዮሃንስ እንደተሰዉ፣ ስልጣን የሙዝ ልጣጭ አዳልጥዋት ተንሸራትታ ሽዋ ገባች። በመተማ ጦርነት የ ተጋሩን ጦር እንዲሰልል የተላከው የሸዋው ሰላይ ታድያ ተጋሩ እና ንጉሱ የሆነ ወፈር ያለ፣ ነጭ ነገር ሲበሉ ስላየ ይህን መረጃ ለ ንጉስ ሚኒሊክ ያደርሳል።

-

ይህ ሚስጢረኛ ምግብ ምን ይሆን ብለው የተጨነቁ አፄ ሚኒሊክም እንቅልፍ አጡ፣ ጉዳዩ እረፍት ነሳቸው። ሳይዉሉ ሳያድሩ ሁሉት ኮማንዶ ብርጌድ ወደ አክሱም ልከው ተጋሩን “የምትበሉት ነገር ምንድን ነው?፣ እንዴትስ ይሰራል ብለው?” ጠየቁ። ተጋሩም እንዴት እንደሚሰራ ነገርዋቸው። ሸዋዎቹም የህብስትን ሚስጢር ተምረው አንኮበር ደረሱ። አዝማሪዉም እንዲህ አለ

ህብስት የትግሬ ነው ብሎ ያለው ማነው
ይሄው ዘመን መጥቶ ሽዋም ሊበላው ነው

ተብሎ የህብስትን መምጣት በምድረ ሸዋ ናኘ፤ አፄዉም ህብስት የስልጣናቸው ምሶሶ እንደሚሆን አላጡትም። የህዝቡ ምኞትም ሰማይ ነካ። ይህ ህብስት የተባለው ምግብ ከህብስተ መና ጋር ግንኙነት አለው ስለተባለ እንደ መብል ብቻ ሳይሆን እንደ የግዜር ቡራኬም ይታይ ጀመር፤ ህዝበ ሸዋ ህብስተ መናን በጉጉት መጠበቅ ጀመረች።

-

ሆኖም ጥበቡን ከትግራይ ተምረው ከወራት የበቅሎ ጉዞ በኃላ ሸዋ የደረሱት ባለሞያዎች፣ የሚጣደዉን ጥደው፣ ልጡን አስገብተው ሲያበቁ የእግዝያብሄር ቡራኬ ስላልነበራቸው ህብስቱ ከላይም ከታችም ነዶ፣ የመኃሉ ብቻ የሚበላ ሆኖ ቀረና፣ ህብስት የመስራት እቅዱ ሙሉ በሙሉ ከሸፈ።

-

በዚህ የተናደዱት የግምዣ ቤቱ ኃላፊም “ይሄ ህብስት አይደለም፣ ዳቦ ነው፣ ለዛዉም መደፋት ያለበት ዳቦ” ሲሉ አምቧረቁ። አይ መድፋት እማ ሀጥያት ነው፣ ለ ነዳያን ይሰጥ ተባለና፣ ወደ ቤተ ክርስትያን ተወስዶ ለ ነዳያንና ለድኩማን መስጠት ተጀመረ።ከዛ ግዜ ጀምሮ የከሸፈ ህብስትን የመስራት ሙከራ እስካሁን ባለማቛረጡ እስካሁን ሽዋ ድፎ ዳቦ ይበላል። እኔም ትላንት ይህን የከሸፍ ህብስት የሽዋ ህዝብ አስገድ ዶ ሲያበላኝ ዋለ።
አያቹህ እንዴት ዓይነት የትግራይ ህዝብ መብት ጠባቂ እንደሆንኩ? ሽዋን አፈር አስቃምኳት። እዉነተኛ ልጅ ነኝ።

- - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - -

(ቡም!!!)
እስካሁን ያነበባቹሁት በሙሉ ዉሸት ነው፣ እልም ያለ ዘረኝነት ነው፣ 100 % ኩታራነት ነው።ሰገጥያዊ የብተና ፅሁፍ ነው፣ድህና ነገር ማየት የማይችሉ ሰገጤዎች የሚፅፉት ዓይነት ፁሁፍ ነው ። የጥላቻ አጥር ገንቢዎች የሚሰሩት ስራ ነው።ጥላቻ ቀላል ነው፣ የደንቆሮ መንገድ ስለሆነ ህሊናና እዉቀት አይጠይቅም። ይህ መንገድ ጃዋርነት፡ አግአዝያዊነት፡ ቤተ አማራነት ነዉ፡፡ አንዱን በማንኳሰስ የምታስከብረው መብት የለም፣ ይህ የብሄር ነጋዴዎች ፖለቲካዊ ስልት ብቻ ነው።

ፍቅር የሌለው አይናማ
ዉጦታል እና ጨለማ

ብሎ ብላቴናው ያዘነላቸው ዓይነት ሰዎች የሚፅፉት ፁሁፍ ነው።
-
ስገጥያዊ ታሪክ አፃፃፍ ይህን ይመስላል። አሁን ፌስቡክ ላይ ብቻ ሳይሆን የታሪክና የፖለቲካ ሰነዶች ተብለው በብዛት እየወጡ ያሉት መፃህፍት በይዘት ከላይ ፈጥሬ ከትዛፍኩት ምንም አይለዩም። ይህን ስታነቡ አንዳንዶቻበደስታ፣ ግማሹ በብስጭት የነደደ ይኖራል። ጉዳየ አይደለም። እንዲህ ዓይነት ዘረኛ የፈጠራ ፁሁፍ በሀገራችን ኖርማል እየሆነ ነው።
-
እስካሁን ከማረሻ ያልተላቀቀ፣ ራሱን መመገብ ያቃተው ህዝብ እርሰ በርሱ በ እኔ እበልጣለሁ ሲጠዛጠዝ ስታይ ከማዘንም አልፈህ አንዳንዴ ምናለ ካናዳ ወይም ኖርወይ በተወለድኩ ያስብላል። ግን ብላቴናው እንዳለው

ቢጎድል እንጀራው ከመሶቡ ላይ
እናት በሌላ ይቀየራ ወይ
ይዤ አላነሳም እጄን ከቀሚሷ
እናት እኮ ናት ተስፋ አልቆርጥም በርሷ

ነዉና ነገሩ ሰገጤነትን እየተፋልም እንኖራለን። ከሚያለያየን ነገር አንድ እሚያደርገን ይበዛል፣ የልዩነት ነጥቦችን እያጎሉ የጋራ እሴቶቻችንን ሊንዱ የተነሱ ሰገጤዎችን ልቦና ይስጣቸው። ኢትዮጵያ ሲባል እሚያንቀጠቅጠው፣ ቁርጥማት እሚይዘው ካለ ግን በሽታው ገዳይ የቢጫ ወባ ሊሆን ስለሚችል በቶሎ ይመርመር።

ተዉኝ ይዉጣልኝ ልጥራት ደጋግሜ
ኢትዮጵያ ማለት ለኔ አይደል ወይ ስሜ

ኣንዳንድ ወዳጆቼ ቴዲን ለመተቸት “ሀገር መዉደድ የሚገለፀም በስራ ነው” ሲሉ ሰማሁ፤ ልክ ናቸው። አንድ ነገር ግን ረስቷል፤ ቴዲ ዘፋኝ ነው፤ ስለሆንም ዘፈን ስራው ነው፤ በስራው ደግሞ ሀገሩን አሞገሰ። የማንም ኩታራ ጥላቻ፣ ልዩነት፣ መበላላት እያዜመ በህዝቦች መኃል የክፋት አጥር በሚያበጅበት ሰዓት ቴዲ አጥሮችን ደረማምሶ የጋራ እሴቶቻችን አጉልቶ “እናት እኮ ናት ተስፋ አልቆርጥም በርሷ” እያለ ሀገሬን ከፍታ ላይ ሰቀላት። እኔም ይሄው ሀገሬ እያልኩ ስጨፍር አደርኩኝ። ይመችህ ቴዲ!!

-

ሸነግ በሰገጤዎች መቃብር ያብባል!!

No comments:

Post a Comment

“በነውጠኛ አብዮት ሳይሆን፣ በማህበራዊ ለውጥ እንታመናለን!”