ልኡል ዘ ወልደ ከ "ቼ በለው!" ( ቼ በለው - Che Belew) መጽሃፍ ላይ Gender - of the Urban context የተሠኘውን፣ በጣም ብዙ ሰዎች ኢሞሽናል ሆነው የወደዱት የኂሩት ያለበትን ቀደዳዊ አጭር ልብ ወለድ እንዲህ አድርጎ ሪቪው አድርጎታል፡፡
-
ልኡል www.leoulzewelde.wordpress.com የተሰኘ ብሎግ አለው፡፡
-
ቼ በለው ገበያው ላይ በደንብ ገብቷል፣ ተደጋሞም ታትሟል፡፡ በወፍ ዘለል ሳምፕሊንግ ከሄድን መጽሃፉን ገዝተው ካነበቡት ውስጥ ወደ 95 ከመቶ የሚሆኑት ወድደውታል፡፡ የመጬ ተመችቷቸዋል፡፡ቼ በለውን ለማንበብ የከተማውን አዟሪዎችን ብትጠይቅ ታገኘዋለህ፡፡ ካልሆነም በከተማው ያሉ ዋና ዋና መጽሃፍት ቤቶች ውስጥ ታገኘዋለህ፡፡
-
ቼ በለውንማ ገዝተህ ማንበብ አለብህ፣ ከምር! And please like the book's Page, ቼ በለው - Che Belew,
Thanks ahead ...
-
Je vous remercie ብለናል፣ ጓድ Leoul Zewelde
-
-
-
-
-
(ፆታዊ ክህደት - የኂሩት ሴታዊ ፅናት)
* * * * *
[ ዳሰሳ - በልዑል ዘወልደ ]
መፅሐፍ - ቼ በለው - ከገፅ 16-21 ማንበብ
Gender - of the Urban context
ደራሲ - እዮብ ምህረትአብ ዮሐንስ
ዋጋ - 60 ብር
-
" Gender - of the Urban context " - ይሄ ቀደዳ ቼበለው መፅሐፍ ላይ ሁለተኛውን ምዕራፍ ይዞ ይገኛል ። መፅሐፉ በባለፈው አመት በእዮብ ምህረተአብ የተፃፈና የእንደወረደ ወሬ ይዘት ያለው የአጫጭር ቀደዳዎች መድብል ነው ።
በዚህ ከላይ በርዕሳችን በጠቀስነው ምዕራፍ ስር ከዘጠኝ መቶ በላይ አማርኛ ቃላት ፤ 78 በእንግሊዘኛ የተተየቡ ቃላት (ርዕሱን ሳያካትት) ፤ ሀያ አንድ በቅርፅ የሚለያዩ አንቀፆች ተካተዋል ።
አብዛኞቹ የተገለፁት ቦታዎች 'እዚህ' የሚል ትርጓሜ ሲኖራቸው ሁለተኛ ዲግሪዋን ለመስራት ከሀገር ውጪ እንደወጣች በአንድ ቃል ብቻ ታትቷል ። ሙሉ አተራረኩም መሳጭ የገላጭ 'Descriptive narration' ዘይቤን የተከተለ ነው ።
የሚከተሉት ዘጠኝ ገፀባህሪያት እንደአመጣጣቸው በቅደም ተከተላቸው በቀደዳው ተሰድረዋል ። አቶ ደሙ - ኂሩት (ዋና) - የመጀመሪያ ፍቅረኛዋ - የልብ ሴት ጓደኛዋ - ፌሚኒስት ጓደኞቿ - ሁለተኛ ፍቅረኛዋ - ሶስተኛው ፈረንጅ ፍቅረኛ - አንዱ ተብሎ ማንነቱ የተሰወረ (የወለደችለትና አራተኛዋ ወንድ ሊሆን የሚችል ) - እንዲሁም እራሱ ደራሲው ናቸው ።
-
(. . . መግቢያ)
በመግቢያው ላይ የዋና ገፀባህሪዋን ኂሩት ቅድመ ታሪክ ጨምሮ የተለያዩ ማንነቶች ፣ ፀባዮችና የፀባይ ለውጦች በየተራ ሲተዋወቁንና ሲገለጡ እናያለን ። ምርቃት - ምክር - ጭዋነት - ጉብዝና - ታታሪነት - ሰው ሰሚነት - ንፁህ አፍቃሪነት - መሰዋዕትነት - ክህደት/መከዳት - እያወቁ አላዋቂ መሆን - ተንኮል - ንዴት - ፀፀት የመሳሰሉት ወደተፈለገው ዋና ታሪክ ማለትም በሶስቱ ምሰሶዎችን ውስጥ ባሉ ተሞክሮና ግብረመልስ እያዋዛ ያንደረድረናል ።
በታሪኩ መጀመሪያ አቶ ደሙ የቤቷ ምርቃት ላይ ተገኝተው ዲስኩር ሲያቀርቡ ሳለ እንዲህ የሚል ያልተቋጨ ዓ.ነገር እናገኛለን ።
" ምንም ቢሆን ሴት ልጅ ያለባል . . ."
( አምስተኛ መስመር ላይ )
እንዚህ ነጠብጣቦች ከርዕሱ አወጣጥ ጋር የተገናኘ አውዳዊ ፍቺ ሊኖራቸው ይችላል ። ወይንም አቶ ደሙ ይህን ከማለታቸው በፊት የተጠቀሙትን ዓ.ነገር ያየን እንደሆነ የተወከለው ማህበረሰብ (ከተሜው) ሴት ልጅ ባል እስካላገባች ድረስ ሙሉ ክብር አይኖራትም ብሎ እንደሚያምን ሊያስተላልፍ ፈልጓል ። ይህን እሳቤ መተንተን የዚህ ፅሁፍ አላማ ስላልሆነ ትቼዋለሁ ።
በስድስት ገፆች ውስጥ ከቅድመ ታሪክና መውጫ ውጪ በሶስት አንጓ ወይንም 'የህይወት ኩርባ' ታሪክ የተከፋፈሉ ዋና ዋና ፍጭቶችን እናገኛለን ።
(. . . ሀ)
ኂሩት ከምንም አንስታ ሰው ባደረገችው ወንድ የደረሰባት ክህደትና በእርሷ ላይ ባሳደረው ጠባሳ ወንድ እርም የምትልበት ክፍል ነው - ከዛ አልፋም ትጠላለች።
በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አውድ ሁሉ የወንድ የበላይነት መወገድ ይኖርበታል በማለት አክራሪ ራዲካል ፌሚኒስት ሆና እናያታለን - መሰሎቿን ትወዳጃለች ። ሲቆይና ሌሎች አጋሮቿ ቀስበቀስ ዞር ሲሉና ትዳር ሲይዙ ደግሞ መልሳ ትበረግጋለች - ለምን ? ።
ይህ የሆነው የተነሳችው በጊዜያዊ ጥላቻ እንደመሆኑ የቆመችበት የሴታዊነት ርዕዮት ሞቲቭ አለመደንደን ምክንያት ነው ባይ ነኝ ። ኂሩት መሰረታዊ የወንድ ጥላቻ የለባትም ።
መሰረታዊ የወንድ ጥላቻ መነሾዎች ውስጥ አንዱ( you need to explain this more) ቤተሰብ ውስጥ ያለ የአባት ሁከተኛነት እንደሆነ Dale O'leary " The Gender Agenda: Redefining equality በሚለው መፅሐፉ ይገልፃል ። ይህን ይዘን ወደመጀመሪያው ገፅ የሄድን እንደሆነ ኂሩት ያልተዝረከረከ መልካም ቤተሰብ ውስጥ መወለዷን አበክሮ ይናገራል። ሌላው ለዚህ አሳማኝ ኩነት በተለያዩ ወንዶች የደረሰባት ክህደት በወንድ ላይ ያላት እምነትን ፍቆ ከናካቴው ሲያጠፋው አይታይም ።
(. . . ለ)
በዚህኛው የህይወቷ ኩርባ የመሸነፍ ስሜቷ ሙሉ ለሙሉ ተስፋዋን ወደ ሀይማኖቷ እንድታረግ ያስገድዳታል ። የሷ ቢጤ ጭዋ ሀይማኖተኛ መስሎ በቀረባት ወንድ'ም ዳግም ትከዳለች ። ይሄ የዳግም ክህደት አጋጣሚ በታሪኩ ውስጥ ያለ ሁለተኛ አብይ ግጭት ነው ።
(. . . ሐ)
በሁለቱ የተለያዪ አበሻ ወንዶች የደረሰባት የፍቅር ክህደት የፈረንጅ ጓደኛ እንድትይዝ ምክንያት ሆናት ። ትዳር ሳይዙ አመት መቆየታቸው ምቾት ያልሰጣት ኂሩት ስትደናገጥና ስትቆጣም ይታያል ።
ፈረንጁ በሌላ አበሻ ሴቶች መነሁለሉና ለትዳር ዝግጁ እንዳልሆነ ብሎም ወደነሱ መሄድ እንደጀመረና እንደተለያዩ ታሪኩ ይተርካል ።
ቁጣዋንና ተመርኩዘን ስብዕናዋን የገመገምን እንደሆነ ከሆነ ከግዜ በኋላ የዳበረ ሀይለኛ በላይነት መንፈስ እንዳለባት ያስጠረጥራል ። ከዚህ ቀደም የየነበሩት ሁለት ፍቅረኞቿ የመጀመሪያው በደሞዝም ሆነ በትምህርት ደረጃ ዝቅ ያለና ጭምት ሲሆን ሁለተኛውንም እሺ ያለችው ድኻ የገበሬ ልጅ እንደሆነ እየማለ በነገራት ግዜ ነበር ።
-
የላይኞቹን ሶስት የወንድ ጓደኞቿን በተለያዩ በቬን ኳስ የሳልን እንደሆነ . . .
ሀ ( ከሰባት አመት በኋላ የከዳት- ማጥፋቱን ቢያምንም) ፤
ለ ( በሁለት ወራቸው የከዳት - የተሰወረ ) ፤
ሐ ( አመት ቆይቶ የከዳት - በሰላም የተለያዩ )
ሁሉም የሚገናኙት በክህደታቸው ነው ። እንደ ክህደቱ ቀለም መለያየት የተለያዩ መልሶችን ብትሰጥም መካዷ የሶስቱንም አንጓ ሴማ አንድ ያረገዋል ።
(. . . መ)
" ወለደች ፤ ከማ ? ከ'አንዱ "
ይሄ ኩርባ በመፅሃፉ ያለ የኂሩት ህይወት መደምደሚያ እና የጠቅላላው ታሪክ ፍፃሜ ሲሆን አንዲት መስመር ብቻ ይይዛል ።
በትምህርቷ ጥሩ የነበረችው ኂሩት የመጀመሪያ ጓደኛዋን የያዘችው ሁለተኛ ዲግሪ ተመርቃ ስራ በያዘችበት ወቅት እንደመሆኑ እድሜዋን ከሃያ አምስት በላይ አድርጎ መገመት አይከብድም ። በዚህ ላይ ሰባት አመት ከሁለት ወር ብንደምር ኂሩትን ወደ ሰላሳዎቹ አጋማሽ እናገኛታለን ። ይህ 'መ' ላይ ለደረሰችበት ውሳኔ እንደምክንያት ሊነሳ
ይችላል ።
-
( . . . መውጫ (ድህረ ታሪክ))
መዝጊያው የ'መ'ን ታሪክ ዲስቶርት በማድረግ 'ግን' 'አይበለውና' 'ለመሆኑስ' በሚሉ መላምቶች ደራሲው ይጠመዳል ። ቀደዳ እንደመሆኑ - ደራሲው በታሪኩ ውስጥ እንደልቡ ሲሳተፍ እና አስተያየት ሲሰጥ እናገኘዋለን ።
ሴቶች ትዳር ሳይመሰርቱ ቆይተው ልጅ የመውለጃ ግዜ ቢያልፍባቸው ስለሚገጥማቸው ነገር የሚተነብየው ይሄ ክፍል የሚደርስባትን የስነልቦናና ማህበራዊ ቀውሶች ለመዳሰስ ይሞክራል ። በትምህርታቸውና በሌሎች መስፈርቶች ከሌሎች በጉብዝና ላቅ ያሉ ሴቶች ለምን ቀድመው ትዳር እንደማይመሰርቱም አተኩሮ ይጠይቃል ።