Tuesday, April 25, 2017

ኃያሉ ሠው

     


(ክቡርነታቸው)

-- ከዱሮ ጀምሮ Arrogant ናቸው - እንደ ወይራ፡፡

-- አንዳንድ እሳቤዎቻቸው አለቅጥ የተጋነኑ፣ ሆነ ብሎ ነገር ቆልማሚ እና የአሁንን (የዘመኑን) ነባራዊ እውነታ ባላየ የዘለሉ ናቸው፡፡
 
-- አሁን ላይ ያሉ መልካም መሻሻሎችን በጥቂትም  እውቅና አይሰጡም፡፡

-- አንዳንድ አቋማቸው አይመስጠኝም፣ አልስማማበትም፡፡

(ግን፣ ግን፣ ግን)

-- ክቡርነታቸው ሶስቱንም መንግስታት ወጥረውና ተጋፍጠው ሲቃወሙ ኖረዋል፡፡

-- በሰማንያ ምናምን አመት ዕድሜው ደፍሮ እውቀቱን እና እሳቤውን ሳያሰልስ የሚጽፍ ምሁር ኖሮን አያውቅም፣ የለንምም!

-- የነጮች ሎሌ፣ ወይንም የጽንፈኛው ዳያስፖራ አፈ ቀላጤ ሆነው አያውቁም፤ አሽቄ አይደሉም!!

-- የ65/66ቱን ረሃብ ቀድመው ለዓለም መንግስታት ያሳወቁትና ያጋለጡት እርሳቸው ናቸው፡፡ ጆናታን ድምቢልቢ በሳቸው ሪፖርት መሠረት ነው መጥቶ ዝነኛውን የሆረር ዶክመንተሪ የሠራው፡፡

-- ከጠረፍ ጠረፍ ዞረው መሬት ለክተው የዚህን አገር ካርታ (Atlas) ያዘጋጁ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡

-- “ጦርነት እና ነውጠኛ አብዮት ለዚህች አገር  መፍትሄ አይሆንም፣ ሆኖም አያውቅም” የሚለው ቀጥተኛ አቋማቸው ከጥንት እስካሁን አልተቀየረም፡፡ አንድ ሰው 60 አመት ሙሉ በአቋሙ ወጥ ሲሆን ማየት በራሱ ትልቅ ክላስ ነው፡፡
(መጽሃፎቻቸውንና ጽሁፎቻቸውን በሙሉ አንብበውና ፍረድ!)

-- ያልተዝረከረከ የአመንክዮ (Reasoning) አሰዳደር፣ እንዲሁም ጥልቅ ሃሳብን  በቀላል አማርኛ መግለጥ ለሳቸው የተሠጠ ትልቅ የስነጽሁፍ ክህሎት ነው፡፡ (“. . . ወይ እኔ ቂል ነኝ፣ ወይ እሱ ቂል ነው” የሚል አገላለጽ አይመስጥም?)

-- ከግማሽ ክፍለዘመን በፊት ትልቅ ምሁራዊ መጽሃፍ የጻፈ፣ ከሃምሳ አመት በኋላም ሳይደክም በፌስቡክ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግ ብቸኛው ምሁር እርሳቸው ናቸው!!


(በተለይ፣ በተለይ፣ በተለይ )

‘አገቱኒ’፣ ‘መክሸፍስ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ’ ፣  'አዳፍኔ'፣ 'አደጋ ያንዣበበት የአፍሪቃ ቀንድ' የተባሉትን የቅርብ ጊዜ መጽሃፎቻቸው ተደጋግመው ሊነበቡ የሚገባቸው  A-Must-To-Read-Books ናቸው፡፡ (አንብቦ ስንዴውን ከእንክርዳዱ መለየት ያንተ ፋንታ ነው)

* * * * *

ሸነግ ለፒያሳው ልጅ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም የመልካም ልደት ምኞት መልዕክቷን በታላቅ አክብሮት ታቀርባለች፡፡
እንኳንም ቆዩልን ፕሮፍ!

No comments:

Post a Comment

“በነውጠኛ አብዮት ሳይሆን፣ በማህበራዊ ለውጥ እንታመናለን!”